ማህበረሰባችን በሁሉም የእይታና መመዘኛ ነጥቦች ቢታይ የሚመጥነው ደረጃ ላይ ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። ስለሆነም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያሳተፈና በሰላም፣ በልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አጠቃቀም፣ በማህበረሰባዊ መስተጋብር፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በታሪክ፣ በባህልና ስነ-ጥበብ ወ.ዘ.ተ ዘርፎች በዓላማና ግብ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ በመስራት ህዝባችንን ወደሚመጥነው ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይቻላል። ይህ ካልሆነ ግን ህዝባችን ከፍተኛ ውስብስብ ችግሮችና ፈተናዎች ውስጥ ከመውደቁ ባሻገር በታሪክም በትውልዶችም ከመወቀስ አናመልጥም።
ህዝባችን የገጠመውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የህልውና አደጋዎች በተናጠል መቀልበስ ከባድ በመሆኑ፤ የሃገራችን የሲቪክ ማህበራት አመሰራረትና አሰራር በሚፈቅደው የህግና መመሪያ ማዕቀፍ መሰረት፤ ሁሉን አቀፍ ማህበር መስርቶ መንቀሳቀሱ ለጊዜው አስፈላጊ መሆኑን ታምኖበታል። በመሆኑም በሙያችን፣ በጊዜያችን፣ በጉልበታችንና በገንዘባችን ህዝባችንን ለማገልገል፤ የህዝባችንን ሰላምና ልማት ማዕከል አድርጎ የሚሰራ የበጎ ፈቃድ ማህበር መስርተን መንቀሳቀስ ጀምረናል።
ሁላችንም የማህበርሰብ ውጤቶች ነን። ሸዋ በታሪክም እንደማህበረሰብ ከራሱ አልፎ ለሃገር ታላቅ ዋጋን ከፍሏል። ማህበረሰባችን የከፈለልንን ዋጋ መመለስ እንኳን ባንችል በቀሪው ዘመናችን “አለንልህ” ልንለውና ያቅማችንን ልናገለግለው የሚገባን የመልካምነት፡ከፍ ሲልም ሰው የመሆን የሰውነት መገለጫ ነው።
በጎ ፈቃደኝነት፣ ወንድማማችነት፣ መከባበር፣ ሃቀኛነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ አንድነትን ማጠናከር፣ ሰላምን መሻት፣ ልማትን መደገፍ፣ መዋለ ንዋይን ማፍሰስ፣ አካታችነት፣ መተባበር፣ ግልጽነትና ፣ተጠያቂነት የማህበራችን የእያንዳንዷ እንቅስቃሴና የየዕለት ተግባሮቻችን መርሆች ናቸው። ስለሆነም ያቅማችንን ለማበርከት እንሰባሰብ፣ እንተባበር፣ እንደጋግፍ፤ አንድ ላይ እንቁምና ማህበረሰባችን የተጋረጡበትን አደጋዎች በጋራ እንመክት።
አሳድጎ፣ መክሮ፣ አስተምሮ፣ ያለውን ሁሉ ሰጥቶ ለቁም ነገር ካበቃኝ ማህበረሰብ ጋር ከመቆምና ዝቅ ብዬ በተግባር ከማገልገል በላይ የሚያረካኝ ነገር የለም! የህልውና አደጋ የተጋረጠበትን ማህበረሰቤን ከመደገፍና ከማገልገል በላይ የዜግነትም የሞራልም ግዴታ ያለብኝም አይመስለኝም።
ሰላም እና ልማት ለህዝባችን ለሃገራችን!
ደረጀ ተክለማርያም (MA, MSc, MSc, PhD)
ሸዋ የሰላምና ልማት ማህበር
(ፕሬዚዳንት)
Copyright © 2021 Shewa Peace & Development Association ሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር (ሸዋሰማ) - All Rights Reserved.
Powered by GoDaddy Website Builder